Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል ሀገራት የጉምሩክ አስተዳዳሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳተፈች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሩሲያ ሞስኮ በተካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት የጉምሩክ አስተዳዳሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፋለች፡፡

በጉባኤው በአባል ሀገራቱ መካከል የንግድ ልውውጥን ለማጠናከር፣ ህገወጥ ንግድ እና ድንበር ተሻጋሪ የጉምሩክ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር፣ የቴክኖሎጂ ልህቀትን ለማምጣት፣ የሰው ኃይል ዓቅም ግንባታን ለማጠናከርና የጉምሩክ መረጃዎችን መለዋወጥ በሚቻልበት አግባብ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የአባል ሀገራቱ በተናጠል እውቅና የሚሰጧቸው “ልዩ መብት የተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ድርጅቶች” በሌሎች አባል ሀገራትም እውቅና እንዲሰጣቸውና ተመሳሳይ ጥቅም የሚያገኙበትን አሰራር ለመዘርጋት እንዲቻል የተጀመረውን ስራ ማጠናቀቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ተፈርሟል፡፡

በጉባኤው የተሳተፉት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታም ሰነዱን መፈረማቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

“ልዩ መብት የተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ድርጅቶች” በአለም አቀፍ የንግድ አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑና የተቀመጡ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሆነው ልዩ መብት የተፈቀደላቸው ድርጅቶች ናቸው ተብሏል፡፡

Exit mobile version