የሀገር ውስጥ ዜና

የአየር መንገዱ አስመራ ቅርንጫፍ የሂሳብ ደብተር መታገዱ በረራ ለማቆም አንዱ ምክንያት ነው ተባለ

By ዮሐንስ ደርበው

September 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስመራ ቅርንጫፍ የሂሳብ ደብተር ሙሉ ለሙሉ መታገዱ በረራ ለማቆም አንዱ ምክንያት እንደሆነ ተገለጸ፡፡

አየር መንገዱ ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ በረራውን ከዛሬ ጀምሮ ማቋረጡን ገልፀዋል።

አየር መንገዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በኤርትራ ውስጥ አገልግሎቱን ለመስጠት ባጋጠመው ከአቅም በላይ በሆነ የአሰራር ችግር ምክንያት እንደሆነ አመላክተዋል።

አየር መንገዱ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የአስመራ በረራ ከስድስት ዓመታት በፊት ዳግም ካስጀመረበት ጊዜ አንስቶ የደንበኞችና የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ፍላጎትን ለማሟላት ሲሰራ መቆየቱንም ነው ያስታወሱት።

ለዚህም በተደጋጋሚ ከኤርትራ ሲቪል አሺዬሽን ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ከመፍታት ጀምሮ የየዕለት ምልልስ ቁጥሩን በመጨመር ሳምንትታዊ የበረራ መጠኑ ወደ 15 አድጎ እንደነበር ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ከመንገደኞች ሻንጣ መዘግየት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታት 160 መቀመጫ ባለው አውሮፕላን 100 መንገደኞችን ይዞ እንዲበር መደረጉን ገልፀዋል።

በቅርብ ጊዜም ከሀገሪቱ አቪዬሽን ባለስልጣን ድንገተኛና በቂ ማብራሪያ ያልያዘ ደብዳቤ በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ተመልክተናል ብለዋል።

በተጨማሪም ደብዳቤው በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን በኩል መውጣቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን በኩል በደብዳቤና በስልክ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢደረጉም ምላሽ ማግኘት እንዳልተቻለም ነው አቶ መስፍን ያነሱት፡፡

ችግሩን ለመፍታት መፍትሄዎችን ከማፈላለግ ጎን ለጎን በረራዎችን ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህ መሃል በኤርትራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካይ ገንዘብ ለማስቀመጥ ወደ ባንክ ባቀናበት ጊዜ ገንዘብ ማስቀመጥ እንደማይችል በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በተፃፈ ደብዳቤ መታገዱን ባንኩ መግለጹንም ነው የጠቆሙት።

አየር መንገዱ ይህን ውሳኔ ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ ምላሽ ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለም አስረድተዋል።

ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የአየር መንገዱ የሂሳብ ደብተሩ መዘጋት እንደማይቻል በደብዳቤ ጭምር ብንገልጽም፥ ባንኩ የተላለፈውን ውሳኔ መቀየር እንደማይችል ገልፆልናል ብለዋል።

በዚህን ምክንያት ለ30 ቀናት የአየር መንገዱ ገንዘብ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ መላክ አልተቻለውም ሲሉ ገልጸው፤ በዚህ ምክንያት አየር መንገዱ ለሰራተኞቹና ለተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያዎችን መፈፀም ባለመቻሉ በረራውን ለመሰረዝ መገደዱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞቹን ለማስተናገድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም ከኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በጎ ምላሽ ማግኘት አልቻለም ብለዋል።

በዚህ ምክንያት በመንገደኞች ላይ ለደረሰው መንገላታት ዋና ስራ አስፈጻሚው በአየር መንገዱ ስም ይቅርታ ጠይቀው፥ መንገደኞች በሌሎች አየር መንገዶች እንዲስተናገዱና እንዲጓዙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መመሪያ ማስተላለፉን ገልፀዋል።

ክፍያ ፈፅመው በረራቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ መንገደኞች ገንዘባቸው ተመላሽ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በመራኦል ከድር