አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኤሲያዋን ሀገር ሞንጎሊያን እየጎበኙ ነው፡፡
ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በአለፈው ዓመት የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በፕሬዚዳንት ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን÷ ከዚሁ ውሳኔ ወዲህ ፑቲን ለመጀመሪያ ጊዜ ሞንጎሊያ ገብተዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይም ከእስር ጋር የተያያዘ አሳሳቢ ሁኔታ አለመኖሩን የክሬምሊን ቃል አቃባይ መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ምንም እንኳን የተወሰኑ የሀገሬው ሰዎች “በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የወጣበት ሰው ወደ ሀገራችን ለምን ይመጣል” በሚል ለተቃውሞ ቢወጡም÷ ፕሬዚዳንት ፑቲን ኡላን ባታር ሲደርሱ የሞንጎሊያው አቻቸው ኡካናጊን ኩሬሉስክ ደማቅ አቀባባል አድርገውላቸዋል፡፡
ሞንጎሊያ አብዛኛውን የነዳጅ እና የኤሌክትሪክ ፍጆታዋን የምታገኘው ከሩሲያ መሆኑም ይታወቃል፡፡