አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምና የ2017በጀት ዓመት አቅጣጫን እየገመገመ ነው።
ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት፥የክህሎት ልማት ፣ አቅም ግንባታና ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በዚህም ለ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች በሀገር ውስጥ ለ345 ሺህ ዜጎች ደግሞ በውጭ ሀገራት የስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም አዳዲስ የውጭ ሀገራት የሥራ መዳረሻዎችን ማስፋት ላይ መሠራቱን የገለጹት ሚኒስትሯ ወደ አውሮፓ ሀገራት የሰለጠኑ ዜጎችን ማሠማራት መጀመሩን ማስታወቃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡