አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማታለል ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የፐርፐዝ ብላክ የቦርድ አስፈጻሚን ጨምሮ አምስት ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድንን ያቀረበውን የጥርጣሬ መነሻና የጊዜ ቀጠሮ መነሻንና የተጠርጣሪዎች ጠበቆችን የመከራከሪያ ነጥብ ተመልክቷል።
ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ የፐርፐዝ ብላክ የቦርድ አባልና የቦርድ ዋና ስራ አፈጻሚ ኤርሚያስ ብርሀኑ፣ 2ኛ የድርጅቱ ኦፕሬሽን ኦፊሰር ናቸው የተባሉት ወ/ሮ ኤፋታት (ሶፍያ) ነጋሽ፣ 3ኛ የድርጅቱ ሰራተኛ የሆኑት ብሩክ በነበሩ ደስታ፣ 4ኛ ገበሬ ቲቪ (ቴቪ) ባለሙያ ዋሲሁን ዋጋው እና 5ኛ የቦርድ አባል እና የብሔራዊ ቴያትር ቤት የሴቶች ማህበር ኃላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት ዘይል ኢብራሒም ናቸው።
ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ቤት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን የጥርጣሬ መነሻውን ለችሎቱ አቅርቧል፡፡
በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ መሃል ሜክሲኮ ላይ በ100 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ባለ3 መኝታ መኖሪያ ቤት በ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚሸጥ መሆኑን በሚዲያ በማስተዋወቅ ሰዎች ቤት ለመግዛት በሄዱበት ጊዜ በመጀመሪያ ገንዘቡን አስገቡና ውሉን ትመለከታላችሁ በማለት ከሌሎች ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን አሳሳች ቃላቶችን በመጠቀም፣ ገንዘቡን ካስገቡ በኋላ ግን የአክሲዮን ግዢ ውል እንዲፈርሙ በማድረግ ምንም አይነት የግንባታ ቦታ ባልተረከቡበት ሁኔታ ላይ 2 ቢሊየን 234 ሚሊየን 200 ሺህ ብር በመሰብሰብ ቤቱን ባለማስረከብ እንዲሁም ግማሹን ገንዘብ ወደ ውጭ እንዲሸሽ ተደርጓል በማለት በህዝብ ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን ጠቅሶ የጥርጣሬ መነሻውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።
የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሰነድ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ እንዲያስችለው በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 59 ንዑስ ቁጥር 1 መሰረት የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው የምርመራ ቡድኑ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው፥ ፖሊስ የገለጸው የጥርጣሬ መነሻ የሙስና ወንጀሎችን የማያሟላ ነው በማለት ተከራክረዋል።
ጉዳዩ መታየት ያለበት በፍትሐ-ብሔር እንጂ በወንጀል ሊሆን አይገባም በማለት የተከራከሩ ሲሆን፥ በዚህ ጉዳይ ላይ በዐቃቤ ሕግና በፖሊስ ምርመራ ከጀመረ 3 ወር እንደሞላው ገልጸው፤ አዲስ አስመስሎ በማቅረብ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ መጠየቁ አግባብ አይደለም በማለት ጠበቆች የመከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።
ቀደም ሲል በተለያዩ ሚዲያዎች ማስታወቂያ ሲሰራጭ የነበረው የአክሲዮን ሽያጭ በሚል እንጂ በቤት ሽያጭ አይደለም በማለትም ተከራክረዋል።
በተጨማሪም ሜክሲኮ አካባቢ ለቤት ግንባታ ተብሎ ከቢጂአይ ጋር የሽያጭ ውል ተፈጽሞ እንደነበር የጠቀሱት ጠበቆቹ፥ ከቢጂአይ ጋር በተፈጠረ አለመስማማት የሽያጩ ውል በመሰረዙ ምክንያት ለይዞታ ግዢ የተፈጸመው 1 ቢሊየን ብር እንዲመለስ ተደርጎ በህብረት ባንክ ገንዘቡ መቀመጡን ገልጸዋል።
1ኛ ተጠርጣሪ፥ ቀደም ሲል የድርጅቱ የህግ አማካሪ ብቻ እንደነበረ፤ ከሰኔ 17 በኋላ ግን በቦርድ ስራ አስፈጻሚነት መሾማቸውን ጠቅሰው፤ ከቤት ሽያጭ ጋር የሚያገናኘኝ ነገር የለም በማለት ተከራክረዋል።
4ኛ ተጠርጣሪ በበኩሉ፥ ማስታወቂያው ለኤጀንቶች ይሰራጭ ተብሎ መታዘዙን ተከትሎ ባለው የጋዜጠኝነት ሙያው ስራውን ብቻ መስራቱን ጠቅሶ የዋስትና መብቱ እንዲከበር ጠይቋል።
5ኛ ተጠርጣሪ ወ/ሮ ሰላማዊት ያጋጠማቸው የጤና ዕክል ምክንያት የኬሞ ህክምና ላይ መሆናቸው በጠበቃቸው ተጠቅሶ ፍርድ ቤተ ግምት ውስጥ እንዲያስገባላቸው ተጠይቋል።
በተመሳሳይ የሌሎችም ተጠርጣሪዎች ምንም የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸው በጠበቆቻቸው ተገልጾ፥ የዋስትና ይፈቀድላቸው ጥያቄ ተነስቷል።
መርማሪ ቡድኑ በጠበቆች ለተነሳ መከራከሪያ በሚመለከት መልስ የሰጠ ሲሆን፥ ከተጠርጣሪዎቹ ለቤት ሽያጭ በማለት ለኮሚሽን ገንዘብ ሲቀበሉ የነበሩና በተጠረጠሩበት የማታለል ሙስና ወንጀል ተሳትፎ አላቸው በማለት መልስ ሰጥቷል።
የግራ ቀኙን ክርክርና የሽያጭ ውሉን ከመርማሪ ፖሊስ አስቀርቦ የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በ1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የ14 ቀን ማጣሪያ ጊዜ ለመርማሪ ፖሊስ ፈቅዷል።
4ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት ግን ሚዲያን ተጠቅሞ የሰራው ስራን በሚመለከት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት በቀጥታ ሊቀርብበት የሚገባው ክስ እንጂ ምርመራ ላይ ሆኖ ጊዜ ቀጠሮ ሊጠየቅ እንደማይገባ መደንገኑን ገልጾ፥ ፍርድ ቤቱ ከሀገር እንዳይወጣ እግድ እንዲጣል በማለት በ60 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈታ ፈቅዷል።
5ኛ ተጠርጣሪ ወ/ሮ ሰላማዊት ደግሞ ያጋጠማቸው የጤና ዕክል የሚታይና የህክምና ማስረጃ ያለው መሆኑን በመጥቀስና በእስር ቢቆዩ ለህይወታቸው አስጊ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ የፈቀደላቸው ሲሆን፥ መርማሪ ፖሊስ ግን ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጾ ዋስትናው እንዲታገድ ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም እስከ የፊታችን ረቡዕ ይግባኙን እንዲያቀርብ በማለት ዋስትናው እስከዚያ ታግዶ እንደሚቆይ አብራርቷል።
በታሪክ አዱኛ