Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አምባሳደር ባጫ ደበሌ ምሥራቅ ዕዝ ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት ሀገር ዋስትና መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምሥራቅ ዕዝ ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር መስዋዕት ለመክፈል ወደኋላ የማይሉ የሠራዊት አባላት ያሉበት ክፍል ነው ሲሉ የቀድሞ የዕዙ አዛዥ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ገለጹ፡፡

ዕዙ የተቋቋመው የሶማሊያን ወረራ ለመከላከል እና ሉዓላዊነትን ለማስከበር እንደነበር አስታውሰው÷ በወቅቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በታላቅ ጀግንነት ከሌሎች የሠራዊቱ አሃዶች እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ ወራሪውን ኃይል አሳፍሮ መመለሱን አውስተዋል፡፡

ዕዙ በሀገር ውስጥ በሐረሪና ሶማሌ ክልሎች፣ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ አርሲ እና ባሌ ዞኖች ይፈጠሩ የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በወሰደው እልህ አስጨራሽ የፀረ-ሽምቅ ተጋድሎ አካባቢዎቹ አሁን ለሚገኙበት ሰላም እና ዕድገት የራሱን አስተዋፅኦ ስለማበርከቱም ጠቅሰዋል፡፡

በወቅቱ የኤርትራን ወረራ ተከትሎም ወደ ቡሬ በመሄድ ከሌሎች ዕዞች እና ክፍሎች ጋር ተሳስሮ የተቃጣውን ወረራ ድል በማድረግ ወደ ሰላም ስምምነት እንዲመጣ ምክንያት የሆነ ከፍተኛ ድል አስመዝግቧል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ተሰማርቶ የሶማሊያን ሕዝብ እና መንግሥት ከአሸባሪው አልሸባብ እና ሌሎች ጥቃቶች ለመከላከል ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት የከፈለ እና ድል ያስመዘገበ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የምሥራቅ ዕዝ የሰራዊት አባላት በሶማሊያ ያሳዩት ጀግንነት እና ቆራጥነት የኢትዮጵያ ሠራዊት ተምሳሌት መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያስተዋወቀ ነው ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

Exit mobile version