ጤና

የስኳር ህመም አይነቶችና አጋላጭ ምክንያቶች

By amele Demisew

September 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነት በደምስር ውስጥ ያለን ስኳር (ግሉኮስ) በሙሉ በተገቢው መጠን ማመንጨት ሲያቅተው ነው።

በዋናነት አራት የስኳር ህመም አይነቶች አሉ፤ እነሱም አይነት አንድ፣ አይነት ሁለት፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰትና በሌሎች ተዛማጅ ህመሞች የሚመጣ የስኳር ህመም ነው።

ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ (አይነት አንድ እና አይነት ሁለት) ዋና የስኳር አይነቶች ሲሆኑ÷ አይነት አንድ የሚባለው ኢንሱሊን የሚያመነጨው በተለምዶ ቆሽት የሚባለው የሰውነት ክፍል ኢንሱሊን ማመንጨት ሲያቆም የሚከሰት ነው።

ይህ ችግር በዋናነት የሚመጣው የሰውነት የህመም መከላከያ ሥርዓት ያለአግባብ ቆሽት ላይ ጥቃት ሲያሳድር የሚከሰት የስኳር ህመም ሲሆን÷ በተለምዶ ህጻናትና እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው።

አይነት ሁለት የሚባለው ደግሞ በአካባቢ ተጽዕኖዎች ማለትም ጤናማ ባልሆነ የአመጋገብ ሥርዓትና የአኗኗር ዘይቤ፣ ከልክ በላይ በሆነ ውፍረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ነው።

በእነዚህ አካባቢያዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት ቆሽት ተገቢውን ሥራ ለመከወን ይሳነዋል፤ አብዛኛው ወይም 90 በመቶ የስኳር ህመም አይነት ሁለት ውስጥ የሚካተት ነው።

የስኳር ህመም የሚያስከትላቸው ችግሮችም የአንጎል ምት ( ስትሮክ )፣ አይነ ስውርነት፣ የልብ መድከም፣ የኩላሊት መድከም ፣ የእግር መቆረጥእና የቁስል ቶሎ አለመዳን ይጠቀሳሉ፡፡

በቤተሰብ ውስጥ የስኳር ህመም መኖር ፣ ዘረመል ፣ የእድሜ መጨመር በስኳር የመያዝ እድልን የሚጨምሩ ቢሆንም አንዳንድ የአኗኗር ሁኔታዎች ደግሞ ለአይነት ሁለት የስኳር ህመም ተጋላጭነትን ይጨምራሉ፡፡

በተጨማሪም ጤነኛ ያልሆነ የአመጋገብ ስርዓት (በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን ማብዛት)እና አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ ሌሎች አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ህመሙ እንዳይከሰት ጤነኛ አመጋገብ መከተል፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረትን ማስወገድ፣ የሚጠራጠሩ ከሆነ የስኳር መጠንን መለካት እና የህክምና ምክሮችን መከታተል እንደሚመከር የኸልዝ ላይን መረጃ ያሳያል፡፡

የስኳር ህመም በዓለም በየዓመቱ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ ከባድ ህመም ሲሆን÷በህመሙ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡