አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ እና ቻይና በዓየር ንብረት ለውጥና ዘላቂ ልማት ላይ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ፡፡
ታዳሽ ኃይል ላይ የሚታየውን ለውጥ ለማፋጠንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት አፍሪካ እና ቻይና የሻንጋይን ጥረት ተቀላቅለዋል ተብሏል።
‘የሻንጋይ ተግባራዊነት ኢኒሼቲቭ ለዘላቂ የኃይል ሽግግር፣ ለአረንጓዴ ኢንቨስትመንትና ለገንዘብ ድጋፍ’ የተሰኘው አዲሱ ኢኒሼቲቭ የተጀመረው የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም 2024 ጉባዔ ከመጀመሩ አስቀድሞ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ኢኒሼቲቩ፥ ከቅሪተ አካል ወደ ታዳሽ ሃይል የሚደረግ ሽግግር ላይ መሰረት ያደረገ ሲሆን፥ የመንግስት ተወካዮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ነጋዴዎችን ያካተተና በታዳሽ ኃይል መሰረተ ልማት እና ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እንዲሁም ፖሊሲዎችን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።
የሻንጋይ ኢኒሼቲቭ ቻይና እና አፍሪካ አብረው እንዲሰሩ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዳቀረበ ተገልጿል፡፡
በዚህም በፖሊሲ ላይ የሚደረገውን ውይይት ማጠናከርን ጨምሮ ለዘላቂ ኃይል የጋራ ምርምር ማድረግና የታዳሽ ኃይል የፋይናንስ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ማስተዋወቅን ያካተተ ነው ተብሎለታል፡፡
በዚህም አፍሪካ እና ቻይና በዓየር ንብረት ለውጥና ዘላቂ ልማት ላይ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን መግለጻቸውን የዘገበው ቲቪ ብሪክስ ነው፡፡