አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሩሲያ ሲሰልል ነበር የተባለ ዓሳ ነባሪ በኖርዌይ የባህር ዳርቻ ሞቶ መገኘቱ ተሰምቷል፡፡
ዓሳ ነባሪው ከኖርዌይ ቋንቋ “ህቫለ” ወይንም “ዓሳ ነባሪ” የሚለውን ወስዶ የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ስም በማከል “ህቫልዲሚር” የሚል ቅጽል ስም እንዳለው ተገልጿል፡፡
ህቫልዲሚር በሩሲያ በሰላይነት ሰልጥኗል ተብሎ የተጠረጠረ ሲሆን፥ ህይወት አልባ አካሉ በደቡብ ምዕራብ ሪሳቪካ ከተማ ተንሳፍፎ ተገኝቷል ነው የተባለው፡፡
በዚህም ለምርመራ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ወደብ መወሰዱ ተሰምቷል፡፡
ዓሣ ነባሪው ለመጀመሪያ ጊዜ በኖርዌይ ውሃ ውስጥ የታየው ከአምስት ዓመት በፊት ሲሆን፥ በአካሉ ላይ የተገጠመ ካሜራ ላይ ‘የሴንት ፒተርስበርግ መሳሪያዎች’ የሚል ጽሁፍ እንደነበረበትም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም ይህ አጥቢ እንስሳ ሰላይ ሊሆን እንደሚችል በብዙዎች ግምት ተሰጥቶበታል ተብሏል፡፡
የሃቫልዲሚር ህይወት አልባ አካል በሣምንቱ መጨረሻ ላይ ማሪን ማይንድ በተሰኘ ድርጅት የተገኘ ሲሆን፥ ድርጅቱ የዓሳ ነባሪውን እንቅስቃሴ ለዓመታት ሲከታተል መቆየቱ ተገልጿል።
የድርጅቱ መስራች ሴባስቲያን ስትራንድ በበኩላቸው፥ የሞቱ ምክንያት ያልታወቀና አካሉ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ያልደረሰበት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የቤሉጋ ዓሳ ነባሪ ዝርያ አማካኝ በህይወት የመኖር ዕድሜ 35 እስከ 50 ዓመት ቢሆንም የሃቫልዲሚር ዕድሜ 15 ዓመት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ሩሲያ ስለዚህ ጉዳይ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥባለች ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡