አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በአመት 5 ነጥብ 4 በመቶ የከተሞች እድገት እንደሚታይ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።
ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ እንደገለጹት ÷በኢትዮጵያ ያለው የገጠርና ከተማ ምጥጥን አነስተኛ ሲሆን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ማህበረሰብ በገጠር ይኖራል።
ከአደጉት አገሮች ጋር ሲነጻጸር በኢትዮጵያ ያለው የገጠርና ከተማ ነዋሪ ምጣኔ አነስተኛ ቢሆንም አሁን ላይ ከተሞች በፍጥነት እያደጉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በአመት 5 ነጥብ 4 በመቶ የከተሞች እድገት እንደሚታይ ገልጸው እድገቱ የከተማና ገጠር ምጥጥንን የሚቀይር ማሳያ እንደሆነ አብራርተዋል።
ይህም በከተማ የሚኖረው ህዝብ እያደገ የሚሄድበትና ለአገር ውስጥ አመታዊ ምርት (ጂዲፒ) እንዲሁም አጠቃላይ የምጣኔ ሃብት እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግበትን እድል ይፈጥራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ ከተሞችን ምቹ የመኖሪያ፣ የመንቀሳቀሻ፣ የምርታማናት አካባቢ በማድረግ የምጣኔ ሃብት ማዕከል ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም ለማስተናገድ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ገልፀው መድረኩ ከተሞችን የሚያነቃቃና ለከተሞች እድገት አቅጣጫ የሚቀመጥበት እንደሆነ ተናግረዋል።