Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቻይና-አፍሪካ ትብብር ጉባዔ የደቡብ ሀገራትን የጋራ ልማት እንደሚያጠናክር ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና-አፍሪካ ትብብር ጉባዔ የደቡብ ሀገራትን የጋራ ልማት እንደሚያጠናከር የቻይና መንግሥት ገለጸ፡፡

በፈረንጆቹ መስከረም 4 እስከ 6 ቀን 2024 የቻይና-አፍሪካ የትብብር ጉባዔ በቤጂንግ የሚካሄድ ሲሆን÷ በጉባዔው ቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት ወዳጅነታቸውን እና ተጨማሪ የትብብር መስኮችን እንደሚያድሱ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ጉባዔው የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ እና የጋራ ራዕይ ያለው የቻይና-አፍሪካ የጋራ ማኅበረሰብ ለመገንባት ያስችላል መባሉን ዥንዋ ዘግቧል፡፡

የቻይና ኢንተርፕራይዞች በአፍሪካ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና አቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በክኅሎት ማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ዘገባው አመላክቷል፡፡

ቻይና የንፁህ መጠት ውኃ እና የኃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶችን በመገንባት የአፍሪካ ሀገራት የፀሐይ፣ የውኃ እና የንፋስ ኃይልን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም እንዲችሉ ማድረጓንም አስታውሷል፡፡

በአንጻሩ ቻይና ከኢትዮጵያ የቡና ምርትን፣ ከደቡብ አፍሪካ ወይን፣ ከሴኔጋል የመዋቢያ ምርቶችን በብዛት እንደምታሰገባ ነው የተመላከተው፡፡

በፈረንጆቹ 2023 ቻይና ከአፍሪካ ጋር የነበራት የንግድ ልውውጥ 282 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር መድረሱ ተጠቁሟል፡፡

Exit mobile version