የሀገር ውስጥ ዜና

ልዩ ልዩ የዐውደ ውጊያ መሣሪያዎችን የሚያሳይ ዐውደ-ርዕይ ተከፈተ

By Mikias Ayele

September 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ልዩ ልዩ የዐውደ-ውጊያ መሣሪያዎችን የሚያሳይ ዐውደ-ርዕይ ክፍት አደረገ።

በሐረር ከተማ በሚገኘው የምሥራቅ ዕዝ ወታደራዊ ሙዚዬም የተዘጋጀውን ዐውደ-ርዕይ የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ እና የመከላከያ የቅርስ ጥናትና አሥተዳደር ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ ዳቼ ከፍተውታል።

በዐውደ ርዕዩ ለዕይታ የበቁት ዕዙ ሲጠቀምባቸው የነበሩና በተለያየ ጊዜ ከጠላት የተማረኩ ከባድና የቡድን የጦር መሳሪያዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እንዲሁም የስፖርት መጫወቻዎችና የሙዚቃ መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች ዕዙ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ የተናጠል የጦር መሳሪያዎችና ሌሎች ቅርሶች ለጉብኝቱ ክፍት ሆነዋል።

የዕዙ የምስረታ በዓል የልማት ሥራዎችን በመጎብኘት፣ በሙዚዬም ርዕይና ሌሎች ዝግጅቶች እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም ይከበራል፡፡