አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን ሁለተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የማስተዋወቅ አካል የሆነውን የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል፡፡
የጽዳት ዘመቻው ኢስላማባድ ዙሪያ በሚገኝ ማርጋላ ሂል ፓርክ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ወጣቶች፣ የማህበረሳብ አንቂዎች፣ የአየር ንብረት ተቆርቋሪዎች፣ ምሁራንና የሚዲያ አካላት በተገኙበት ነው የተካሄደው፡፡
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ዘመቻው ውብና ጽዱ አካባቢ ለመፍጠር ብሎም ኢትዮጵያ ያላትን ምርጥ ተሞክሮና ልምድ ለፓኪስታን ለማስገንዘብ ያለመ ነው፡፡
አክለውም የአምስት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር ስኬት፤ በዚህ ዓመትም 600 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀምበር የመትከል መርሐ-ግብር በአመረቂ ሁኔታ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
የችግኝ ተከላው የሀገሪቱን የአረንጓዴ ሽፋን ማሳደጉን፣ የአየር ንብረት ለውጥን እየተከላከለና ከፍተኛ የሥራ እድል እየፈጠረ መሆኑን እንዲሁም ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻልና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አምባሳደሩ በስኬት ለተጠናቀቀው የጽዳት ዘመቻ ተሳታፊዎችን አመስግነው፥የእውቅና እና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡