አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዘርፎች ለሚሰማሩ አልሚዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ኤኤምጂ ሆልዲንግስ በሸገር ከተማ ገላን ክ/ከተማ ለሚያስገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ከ7 የሕንድና ቻይና ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
በፊርማ ሥነ- ሥርዓቱ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተገኝተዋል፡፡
አቶ ሽመልስ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈለጊው ድጋፍ ይደረጋል፡፡
ኤኤምጂ ሆልዲንግስ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም አውስተዋል፡፡
አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው÷አምራች ዘርፉን ተወዳዳሪ፣ ውጤታማ እና ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን በትኩረትና በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር በማስተሳሰር ዘላቂ ኢንዱስትሪ መገንባት ላይ መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ተኪ ምርቶችን ለመጨመር እና ወጪ ንግድን ለማሳደግ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ተቋማቱ በኬሚካል ዘርፍ፣ በአውቶሞቲቭ፣ በኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ግብዓቶች፣ በብረታ ብረትና ሌሎች ዘርፎች በጋራ እንደሚሰሩ ተመላክቷል፡፡
በብርሃን ደሳለኝ እና ሳዕዳ ጌታቸው