Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአስገዳጅ የብሔራዊ የምግብ ማበልጸግ ፕሮግራም ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከዛሬ ጀምሮ ወደ ስራ የሚገባ አስገዳጅ የብሔራዊ የምግብ ማበልጸግ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ፕሮግራሙን ይፋ የማድረጊያ እና የአምስት አመት ስትራቴጂ እቅድ ማስተዋወቂያ መድረክ አካሂዷል።

ፕሮግራሙ በምግብ ዘይት፣ በስንዴ ዱቄትና በጨው ምርት ላይ የሚተገበር ሲሆን÷ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችንም እንደሚጨምር ተገልጿል።

አስገዳጅ ስርዓቱ ፋብካሪዎች በምግብ ዘይት፣ በስንዴ ዱቄትና የጨው ምርትን በቫይታሚንና ማዕድን የበለጸጉ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በአዕምሮው የዳበረና ምርታማ የሆነ ትውልድ ለማፍራት በንጥረ ነገር የበለጸገ ምግብ ለዜጎች ማቅረብ ይገባል።

ከአመጋገብ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የሕብረተሰብ የጤና ችግሮችን መፍትሔ ለማበጀት ከተነደፉ ስትራቴጂዎች መካከል የብሔራዊ ምግብ ማበልጸግ ፕሮግራም አንዱ ነው ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕጻናት መካከል በተመጣጠነ ምግብ እጥረት 39 በመቶው የሚሆኑት የመቀንጨር ችግር ያጋጥማቸዋል ብለዋል።

11 በመቶው የሚሆኑት የመቀጨጭ እንዲሁም 22 በመቶው የሚሆኑት ደግሞ የክብደት መቀነስ ችግር እንደሚያጋጥማቸውም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version