ቴክ

በኢኖቬቨንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተገኘው የኢኮኖሚ እድገት የሚበረታታ ነው ተባለ

By Shambel Mihret

August 31, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢኖቬቨንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በመሰማራት የተገኘው የኢኮኖሚ እድገትና የተፈጠረው የስራ እድል የሚደነቅና የሚበረታታ መሆኑን የኢኖቬቨንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በበለጠ ሞላ (ዶ/ር) የተመራ ቡድን በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠር ላይ ያሉ ስታርትአፖችን ጎብኝቷል፡፡

ቡድኑ በአይሲቲ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ኤሮስፔስ ላይ የተሰማራውን ፋሪስ የቴክኖሎጂ ድርጅት እና ዘ- ሞል የተባለውን ፕላትፎርም በመጠቀም በምግብ አቅርቦት እና የተለያዩ ስራወችን የሚሰራ የስታርትአፕ ድርጅቶችን ጎብኝቷል።

ጉብኝቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስታርትአፖችንና የኢንኩቤሽን ማዕከላት የተሻለ አቅም በመፍጠር ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል በቅርበት ስራቸውን ለመጎብኘትና ለማበረታታት እንዲሁም ተግዳሮቶቻቸውን ለመለየት ያለመ ነው፡፡

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በወቅቱ÷ ኢትዮጵያ ያላትን አቅምና ሀብቷን ወደ ውጤት ቀይራ የምትጠቀምበትና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ሰፊ ኢኮኖሚ ፈጥራ ተጠቃሚነትን የምታረጋግጥበት ጊዜ እየመጣ መሆኑን ስታርትአፖቹ ያሉበት ደረጃ ያሳያል ብለዋል።

በዘርፉ ላይ በመሰማራት የተገኘው የኢኮኖሚ እድገትና የተፈጠረው የስራ እድል የሚበረታታ መሆኑንም ገልፀዋል።

ስታርትአፖቹ ሀብታቸውን ተጠቅመው ውጤት ለማስመዝገብ ከዚህ በላይ መፍጠን አለባቸው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡