አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ለሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ 100 ሚሊየን ዶላር በጀት መልቀቁን አስታወቀ።
በተመድ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ፈንድ (ዩኤንሲኢአርኤፍ) በኩል የተለቀቀው በጀት የሰብዓዊ ቀውስን ለመፍታት የገንዘብ እጥረት ላጋጠማቸው አካላት ተደራሽ የሚሆን መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ አህጉራት የሚገኙ 10 ሀገሮች በጀቱ የሚደርሳቸው መሆኑን ተመድ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የበጀት እጥረት የህይወት አድን ስራ የሚሰሩ ድርጅቶችን ማደናቀፉ አሳዛኝ መሆኑን የገለጹት የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮችና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ አስተባባሪ ጆይስ ምሱያ፤ ዩኤንሲኢአርኤፍ የሚያጋጥመውን የበጀት እጥረት ለመፍታት ለጋሾች ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
አሁን ከተለቀቀው 100 ሚሊየን ዶላር ውስጥ አንድ ሶስተኛው በተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) በኩል አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተደራሽ እንደሚሆን ጠቁመው፤ በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ የከፋ ጉዳት ያደረሰባቸው ሀገራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ፣ ካሜሩን፣ ሞዛምቢክ፣ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቡሩንዲ፣ ማላዊ፣ የመን፣ ማይናማር እና ሄይቲ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
በተመድ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ፈንድ በኩል ይህ በጀት ሲለቀቅ ከየካቲት ወር ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ቢሆንም፤ ቀደም ካሉት ሶስት ዓመታት አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል።
በመላው ዓለም ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን 187 ሚሊየን ሰዎች ለመድረስ 49 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልግ ቢሆንም ማሟላት የተቻለው የፍላጎቱን 29 በመቶ ብቻ እንደሆነ ያመለከተው ተመድ፤ የ35 ቢሊየን ዶላር ክፍተት እንዳለበት ጠቁሟል።