አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፐርፐዝ ብላክ ኢ ቲ ኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚዎች ስልጣንን አለአግባብ በመገልገል እና ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው ዛሬ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በማኅበሩ ተጭበርብረናል ያሉ ባለአክሲዮኖች ለፖሊስ ባቀረቡት አቤቱታ መነሻነት ምርመራ ተጀምሮ የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎች ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ማኅበሩ መሀል ሜክሲኮ ላይ ገና በእጁ ባላስገባው መሬት እና ይዞታ ቤት ገንብቶ ባለ ሦስት መኝታ አፓርትመንት በ1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚሸጥ መሆኑን በሚዲያ እና በራሪ ወረቀቶች በማስተዋወቅ ከሕዝቡ ገንዘብ ሲሰበስብ መቆየቱን በተለያየ መንገድ ከሕብረተሰቡ ሲቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎች ያመላክታሉ፡፡
በዚህ መነሻም ሥራ አስፈጻሚዎቹ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም በቀጣይ ዝርዝር ጉዳዩን ተከታትሎ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡
በታሪክ አዱኛ