አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከነገ ጀምሮ ለ6 ቀናት እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ ቀደም ሲል በክልሉ 7 ዞኖች እና 3 ልዩ ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልየታ መከናወኑን አስታውሰዋል።
ነገ በሆሳዕና ከተማ በሚጀመረው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የምክክር መድረክ ደግሞ ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የተመረጡ የህብረተሰብ ወኪሎች፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት፣ የልዩ ልዩ ማህበራትና ተቋማት፣ የፓለቲካ ፓርቲዎችና የታዋቂ ግለሰቦች ተወካዮችን ጨምሮ ከ1ሺ 700 በላይ ወኪሎች በአጀንዳ ልየታው ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።
ተሳታፊዎች ምክክሩ የሚኖረውን ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት በንቃት እንዲሳተፉም ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) ጥሪ ማቅረባቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡