የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ከ12 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ይጠበቃል

By Feven Bishaw

August 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ከ12 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለፀ፡፡

በትምህርት ዘመኑ ከቅድመ መደበኛ እስከ ኮሌጆች ድረስ በ37 ሺህ 959 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደት እንደሚከናወን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ግርማ ባይሳ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ከ12 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

በክረምቱ ወቅትም 1 ሺህ 939 የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን፣ ከ6 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎች መጠገናቸውን እና 1 ሺህ 114 ቤተ-መጻሕፍት ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የ2017 ትምህርት ዘመን ምዝገባ ከነሐሴ 27 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚከናወን እና የመማር ማስተማር ሂደቱ መስከረም 7 እንደሚጀመርም አስታውቀዋል፡፡