አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የሚከሰቱ ወረርሽኞችንና ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
በብራዛቪል ኮንጎ እየተካሄደ ያለው 74ኛው የአፍሪካ አህጉር የዓለም ጤና ድርጅት መድረክ እንደቀጠለ ነው፡፡
በመድረኩ በአፍሪካ በተለያዩ ጊዜያት ወረርሽኞችና ሌሎች ድንገተኛ የጤና አደጋዎች እየተከሰቱ የማህበረሰቡ ጤና ስጋት መሆናቸው አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል።
ኢቦላ፣ ኮቪድ 19 እና ሌሎች ወረርሽኞች በአፍሪካ ቀጠና ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን በማስታወስ አሁን ላይ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የደቀነው የጤና አደጋ በተለይ ለአፍሪካ አሳሳቢ መሆኑ ተነስቷል።
ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት÷እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተጠረጠረም ሆነ የተያዘ ሰው አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
በሽታው እንዳይከሰት ፣ከተከሰተም ለመቆጣጠር የሚያስችል ሰፊ የቅደመ መከላከልና ቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአፍሪካ የሚከሰቱ ወረርሽኞችንና ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር “ለአፍርካ ችግር የአፍርካ መፍትሄ” በሚል መርህ ሀገራት በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወርሽኞችንም ሆነ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በዘርፉ የሚደረግ ኢንቨስትመንትን መደገፍ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡