አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የዳኝነት ልዑካን ቡድን እና በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከል ዛሬ የልምድ ልውውጥ ተደርጓል፡፡
በመርሐ ግብሩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አበባ እምቢአለና፣ የሻይንጋይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ጉዎ ዎይኪንግና በቻይና በዳኝነት አካል የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ዋና ዋና የለውጥ ስራዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ገለጻ ተደርጓል።
በተለይም የፍርድ ቤትን አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ ከማድግ አኳያ በተሰሩ ስራዎች እና በፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳዳር ዘርፍ ትኩረት በሚሹ የለውጥ ስራዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
የቻይና ልዑካን ቡድንም የሀገራቸውን ተሞክሮ ያካፈሉ ሲሆን÷ የሁለቱን ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ መነሻ በማድረግ በዳኝነቱ ዘርፍ በተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ላይ በትብብር ለመስራት የልምድ ልውውጡ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ልዑኩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የዋይድ ኤርያ ኔትወርክ ዳታ ሴንተርና የስማርት ኮርት ሩም የቴክኖሎጂ ስራዎችን መጎብኘታቸውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡