አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስን 1 ለ 0 በማሸነፍ የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ሀገራት ሻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደ የፍፃሜ ጨዋታ ሴናፍ ዋቁማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የማሸነፊያ እና ብቸኛ ግብ ከመረብ አሳርፋለች፡፡
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከነሐሴ 11 ቀን 2016ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው በዚህ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ተወካዩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሸነፉን ተከትሎ የሴካፋ ዞንን በመወከል በካፍ የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፍ ይሆናል፡፡
ሴናፍ ዋቁማ በስድስት ጎሎች የሻምፒዮኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆናለች፡፡
ቀደም ብሎ ከቀኑ 5ሰዓት በተካሄደ የደረጃ ጨዋታ የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ የታንዛኒያውን ሲምባ ኩዊንስን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ውድድሩን በሦስተኛነት አጠናቅቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በ2013ዓ.ም ኬንያ ባስተናገደችው የመጀመሪያው ውድድር 2ኛ፣ በ2014ቱ የታንዛኒያ ውድድር 3ኛ እንዲሁም በ2015 ዓ.ም ዩጋንዳ ላይ ተደርጎ በነበረው ውድድር 2ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ መሳተፉን አረጋግጧል።