የሀገር ውስጥ ዜና

ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ገለጸች

By Shambel Mihret

August 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷በሀገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና በኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ በትብብር መሥራት በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡

አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ኢትዮጵያና ሩሲያ የረጅም ጊዜ የታሪክ እና የባሕል ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡

በየትኛውም የፈተና ጊዜ ተጠብቆ የቆየው የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ኢትዮጵያ ለምታደርጋቸው ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴዎች ሩሲያ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር ኤቭጌኒ በበኩላቸው ሩሲያ ለኢትዮጵያ የሁልጊዜም አጋር መሆኗን ገልጸው ÷ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ታሪካዊ ግንኙነት መጠናከር ለሚያከናውናቸው ተግባራት ተገቢ ድጋፍ እንደሚደረግ ማረጋገጣቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡