አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ትግበራ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ትልቅ አቅም ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡
“የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ሁነቶች ሲካሄድ የቆየው ልዩ የንግድ ሳምንት ማጠቃለያ መርሐ ግብር የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች በተገኙበት ተካሂዷል።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተዘጋጀው የንግድ ሳምንት ከውጭ የሚገባውን ምርት መተካት፣ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ማስተዋወቅን አላማው አድርጎ የተከናወነ ነው።
በመርሐ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ÷ መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች የግሉ ዘርፍ ሚናን አድንቀው የምርት፣ ንግድና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማዘመን መንግስት የጀመረውን የዲጅታላዜሽን ትግበራ ለማጠናከር የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ጠይቀዋል።
ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ መሳካት በተቀመጡ ምሰሶዎች የግሉ ዘርፍ በሁሉም እንዲሳተፍ መንግስት የሰጠውን እድል አስታውሰው፤ መሰረተ ልማትና የሰላም ጉዳይ ለአምራችና ንግድ ዘርፉ ፈተና እንዳይሆን በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የመንግስትና የግሉን ዘርፍ በጋራ መስራት የሚያጠናክር ውይይትና የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ አምራቾችና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን እውቅና ተሰጥቷል።
በፍሬህይወት ሰፊው