ስፓርት

በአውሮፓ የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ነገ ይዘጋል

By Feven Bishaw

August 29, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሊዘጋ ሰዓታት ሲቀረው ክለቦች ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

የእንግሊዞቹ ክለቦች ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል፣ አርሰናል እና ቼልሲ በመዝጊያው 11ኛ ሰዓት ላይ የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች ለመግዛት ሩጫ ውስጥ ገብተዋል።

የዝውውር ዋጋቸው የተጋነኑ እና አሰልቺ የድርድር ሂደት የነበራቸው ዝውውሮች በ11ኛው ሰዓት ላይ እልባት ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አርሰናል በስፔናዊው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ራያ ቦታውን የተነጠቀውን አሮን ራምስዴል ለሳውዝአምፕተን ለመሸጥ በ25 ሚሊየን ፓውንድ የተስማማ ሲሆን በምትኩ የ23 ዓመቱን ስፔናዊ ግብ ጠባቂ ጆዋን ጋርሲያን ከካታላኑ ክለብ ኢስፓኞል ለማምጣት መቃረቡ ተሰምቷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ አርሰናል በመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል ያልተሳከለትን ዑራጓያዊ አጥቂ ዳርዊን ኑኔዝን በመጨሻው ሰዓት ሊያስኮበልል ይችላልም ተብሏል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ የፊት መስመሩን ለማጠናከር የብሬንትፎርድን አጥቂ ኢቫን ቶኒን በመጨረሻዎቹ ሰዓታት ለማስፈርም 40 ሚሊየን ዩሮ አዘጋጅቷል ተብሏል ።

የ28 አመቱ እንግሊዛዊ አጥቂ በብሬንትፎረድ የቀረው ውል አንድ አመት ብቻ በመሆኑ ክለቡ በመጪው ክረምት ተጫዋቹን በነፃ ላለማጣት ይሸጠዋል ተብሎ ተገምቷል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ቤን ቺልዌልን ከቼልሲ ወደ ቡድኑ ሊቀላቅል እንደሚችል ሲነገር የ24 ዓመቱ ጀደን ሳንቾ ከክለቡ በመልቀቅ ጁቬንቱስን የሚቀላቀል ይሆናል ተብሏል፡፡

በክረምቱ የተጫዋቾች ገበያ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው ቼልሲ ቤልጂየማዊውን አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩ ለናፖሊ ከሸጠ በኋላ በኔፕልስ ደስተኛ ያልሆነውን ናይጄሪያዊ አጥቂ ቪክቶር ኦሲምሄን ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ ለማምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑ ተዘግቧል።

በተጨማሪም ቼልሲ ግብ ጠባቂውን ኬፓ አሪዛ ባላጋ በአንድ አመት የውሰት ውል ለቦርንማውዝ መስጠቱ ሲረጋገጥ በዌስትሃም ዩናይትድ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው አጥቂው ታሚ አብርሃም ለጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ለመፈረም መቃረቡ ተነግሯል ።

ፈረንሳዊው የባየር ሙኒኩ የክንፍ ተጫዋች ኪንግስሌይ ኮማን ወደ ሳውዲ አረቢያው አል ሂላል ሊያመራ እንደሚችል የተነገረ ሲሆን ክለቡ የአል ሂላልን ጥያቄ መቀበሉ እንዲሁም ተጫዎቹም ይሁንታውን መስጠቱ ተሰምቷል።

በነገው እለት በሚዘጋው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያልተገመቱ ዝውውሮች ሊደረጉ እንደሚችሉም ይጠበቃል።