አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ13 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 268 ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት መግባታቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ደምሰው ባቾሬ፤ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም ከ13 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ያስመዘገቡ 268 ባለሃብቶች በግብርና፣ በአገልግሎትና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈቃድ በመውሰድ ወደስራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ከባለሀብቶቹ መካከል በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ 85 የሚሆኑ ባለሃብቶች ከሰባት ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
ወደ ስራ ከገቡ ባለሀብቶች መካከል ማምረት የጀመሩ፣ ግንባታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ያሉና ለምርት እየተዘጋጁ ያሉ መኖራቸውን ገልጸው፤ በዚህም ከ44 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።
በክልሉ ያለውን እምቅ የመልማት አቅም ለመጠቀም ከዚህ ቀደም በተበጣጠሰ መልኩ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰጠውን ቦታ የማስተካከል ስራ መሰራቱን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ለዚህም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ከ1 ሺህ 500 ሄክታር በላይ የኢንዱስትሪ ዞን ተለይቶ ወደ ኢንቨስትመንት ለሚገቡ ባለሀብቶች መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ዘርፉን ለማበረታታ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ ሌሎች አቅርቦቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ወደ ክልሉ የሚመጡ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንም አክለዋል።