አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ-ወጥ መድኃኒቶችንና ምግቦችን በመቆጣጠር ረገድ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ።
በምግብና ጤና ግብዓት ቁጥጥር ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ የሚመክር ዓመታዊ ጉባዔ በድሬዳዋ ተጀምሯል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በመድረኩ እንዳሉት÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ-ወጥ መድኃኒትና ቁጥጥርን በተቀናጀ መንገድ በመከላከል ረገድ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል።
የምግብ ደህንነትና ጥራት እንዲረጋገጥ የተሰሩ ስራዎችም የተሻለ ውጤት ተገኝቶባቸዋል ብለዋል።
ደረጃውን የጠበቀ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት፣ ቅንጅታዊ ስራን በማጠናከር የተሻለ ስራ መስራት የሚያስችሉ ቅደመ ዝግጅቶች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።
ስራዎቹን በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ በማስቀጠል የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ዓመታዊ ጉባዔው ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አውስተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ዓመታዊ ጉባዔ በዘርፉ ትኩረት በተሰጣቸው ስድስት ዋና ዋና ተግባራት ላይ ውይይት እንደሚካሄድ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጉባዔው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የዘርፉ የአመራር አካላት እንዲሁም የጉምሩክ ኮሚሽን እና የፌደራል ፖሊስ አመራር ተሳታፊ ሆነዋል።