አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጎጂ ቤተሰቦች ይነሳ የነበረውን የትራፊክ አደጋ የካሳ ክፍያ ተፈፃሚነትና ፍትሐዊነት ችግር መፍታት የሚያስችል ደንብ ተግባራዊ መደረጉን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርሆ ሀሰን በሰጡት መግለጫ÷ለሚፈጠሩ አደጋዎች ምላሽ ብቻ ሳይሆን ቅድመ ጥንቃቄ ላይም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ አደጋ የመድን ፖሊሲ የአረቦን ተመንና የካሳ መጠን ክፍያን ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንብና የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክን ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ ደንብ ማፅደቁንም አስታውሰዋል።
አቶ በርሆ ሀሰን በመግለጫቸው÷ይህ ተፈፃሚ መሆን መጀመሩ ደግሞ በዘርፉ ያለውን ሰፊ ችግር ለማጥበብ ከግንዛቤ መፍጠር ጀምሮ የሕግ የበላይነትን እስከማስከበርና ምቹ አሰራርን እስከመፍጠር ያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲሱ ደንብ መሠረትም በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት የሚከፈለውን የካሳ መጠን እስከ 250 ሺህ ብር እንዲሆን መደረጉም ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ የሶስተኛ ወገን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን መደረጉም በመግለጫው ተነስቷል።
በአሸናፊ ሽብሩ