አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የኮሪደር ልማቱን ዘላቂነት የሚያረጋግጥ ደንብ አፀደቀ።
ምክር ቤቱ የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤትን እንደገና ለማቋቋም እና አደረጃጀቱን፣ ሥልጣንና ተግባራቱን ለማሻሻል በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
ይህም በከተማው እየተስተዋሉ የሚገኙ የደንብ መተላለፎችንና ተያያዥ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በዘላቂነት ለመከላከል ብሎም ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ቅጣትን ይወስናል መባሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም አግባብ በአላቸው ሕጎች የተመላከቱ የደንብ መተላለፍ ቅጣቶችን በማስፈፀም የከተማዋን ጽዳትና ውበት ለማስጠበቅ ያግዛል ተብሏል፡፡
እንዲሁም የኢንቨስትመንት ቦርድ ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ ደንቡን በማፅደቅ ሥራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።