Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጆሀን ሩፐርት የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቱጃር ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ አፈሪካዊው ጆሀን ሩፐርት የሃብታቸውን መጠን ወደ 14 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በማሳደግ በአፍሪካ ቀዳሚው ቱጃር ለመሆን መብቃታቸው ተነገረ።

የግዙፉ ቅንጡ ሰዓቶች አምራች ሲ ፋይናንሺየር ሪችሞንት ድርጅት ባለቤት የሆኑት የ74 ዓመቱ ሩፐርት የሀብታቸው መጠን በመጨመሩ በአህጉሩ ቀዳሚ ቱጃር ለመሆን በቅተዋል።

ጆሀን ሩፐርት ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቱጃር የነበሩት ናይጄሪያዊውን አሊኮ ዳንጎቴን በመብለጥ ነው የቀዳሚነት ስፍራውን የያዙት።

በአህጉሩ ሁለተኛው ቱጃር የሆኑት አሊኮ ዳንጎቴ የሀብታቸው መጠን 13 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር መሆኑ ተገልጿል።

እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ሌላኛው ደቡብ አፈሪካዊ ቱጃር ኒኪ ኦፕንሄመር በ11 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የአህጉሩ ሶስተኛ ባለሃብት ሲሆኑ ግብፃዊው ናስፍ ሳውሪስ ደግሞ በ9 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር አራተኛው የአህጉሩ ቱጃር ሆነዋል።

Exit mobile version