Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአፋርና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶችን በዘላቂነት የመፍታት ሂደት በተሳካ መልኩ ቀጥሏል – አቶ ብናልፍ አንዷለም

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶችን በዘላቂነት የመፍታት ሂደት በተሳካ መልኩ መቀጠሉን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

ባለፈው ሐምሌ ወር የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ እና የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ የተከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ከስምምነት ደርሰው የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው የመመለስና ለግጭት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በሕገ-መንግሥታዊና ሕጋዊ አሠራር መፍትሔ ለመስጠት ቃል ገብተው እንደነበር ይታወሳል።

በዚህም የአፈጻጸሙን ሁኔታ በሰላም ሚኒስትሩ አስተባባሪነት ከፌዴራልና ከክልሎች የተውጣጣ ልዑክ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች በመገኘት ገምግሟል።

በዚሁ ወቅት አቶ ብናልፍ አንዷለም÷ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል።

በቅድሚያ ግጭትና ሰብዓዊ ጉዳትን ማስቆም እንዲሁም በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው መመለስ በሚል በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

አዋሳኝ አካባቢዎችን ከታጠቁ ኃይሎች እንቅስቃሴ ነፃ በማድረግ የፌዴራል የፀጥታ ኃይል ማሰማራት አንዱ የስምምነቱ አካል ነው በማለት ገልጸው፤ በአካባቢው የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተው ግዴታቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።

የቴክኒክ ቡድኑን በማስተባበር ሲሰሩ የቆዩት የሰላም ሚኒስትሩ አማካሪ ካይዳኪ ገዛኸኝ÷ የጠብ አጫሪነትን እንቅስቃሴ ማስወገድ፣ በነፃ ቀጣናው ገለልተኛ የፀጥታ ኃይል ማሰማራት፣ ውይይትና ዕርቀ-ሰላም፣ ተፈናቃዮችን መመለስና ለግጭት መንስኤ የሆኑ የወሰን ጉዳዮችን ዘላቂ ዕልባት መስጠት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን አንስተዋል።

በስምምነቱ መሠረት ግጭቶችን በማስቆም በሂደት ለሰላማዊ መፍትሔ የሚበጁ መሠረቶች እየተቀመጡ መሆኑን የገለጹ ደግሞ የመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩም ናቸው ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ÷ የዘላቂ ሰላም ሂደቶች በጥሩ ሁኔታ መቀጠላቸውን በመግለጽ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች በደረሱበት ስምምነት መሠረት ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚችሉ ቀጣይ ምዕራፎች የሚከናወኑ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

Exit mobile version