Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በስልጠና ሰበብ 3 ሚሊየን ብር እንዲመዘበር አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ 5 ሰራተኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስቴር ሶስት ዳይሬክተሮችን ጨምሮ አምስት ሰራተኞች በስልጠና ሰበብ 3 ሚሊየን ብር እንዲመዘበር አድርገዋል ተብለው ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ በሚኒስቴሩ የግዢና ፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ አደፍርስ ደሳለኝ፣ 2ኛ የሰላም ግንባታ ማጎልበቻ ዳይሬክተር ወንዶሰን መኮንን፣3ኛ የሰላም ግንባታ አቅም ማጎልበቻ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ መብራቱ ካሳ፣ 4ኛ የግዢ ክፍያ ባለሙያ ወ/ሮ አስካለ ንጉሴ እንዲሁም 5ኛ ወ/ሮ አለምሸት ሞገስ ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ምርመራ መምሪያ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቅርቦ፣ የጥርጣሬ መነሻውን ጠቅሶ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል።
ተጠርጣሪዎቹ የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጋር በመቀናጀት ግንቦት 17 እና 18 ቀን 2014 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ያካሄደውን የምክክር መድረክ መነሻ በማድረግ በሚኒስቴሩ የተመደበው ወጪ 2 ሚሊየን 58 ሺህ 700 ብር ሆኖ እያለ ተጠርጣሪዎቹ የስልጠናውን ደብዳቤ በመቀየር ከግንቦት 16 እስከ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ለ4 ቀናት በማድረግና በስልጠናው ተሳታፊዎችን ቁጥር 350 በማድረግ የስልጠናውን ወጪ 5 ሚሊየን 746 ሺህ 829 ብር ማድረጋቸውን መርማሪ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ላይ የጥርጣሬ መነሻው ገልጿል።
በዚህም በተቋሙና በመንግስት ላይ ያልተገባ ወጪ እንዲኖር በማድረግ ለግላቸው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ 3 ሚሊየን ብር የመንግስትን ገንዘብ ለመመዝበር በመቀናጀት ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀምና የክፍያ ሰነድ አዘጋጅተው ለማስፈረም ሲሞክሩ በበላይ ኃላፊ መያዛቸውን ፖሊስ ጠቅሶ በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጣርቶ መዝገቡን ለሚመለከተው የፍትህ አካል ለመላክ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው÷ ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ በፍትሐብሔር ተከሰው እንደነበር እና በተቋማቸውም በስነምግባር ግድፈት ተቀጥተው እንደነበር በመግለጽ በድጋሚ “ወንጀል ፈጽማችኋል መባላችን ተገቢ አደለም ” በማለት ተከራክረዋል።
ዋስትና እንዲፈቀድላቸውም የጠየቁ ሲሆን÷ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ያልተጠናቀቁ የምርመራ ስራዎችን ሊያደናቅፉ ይችላሉ በማለት የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ የጠየቀው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
የግራ ቀኝ ክርክሩንና የፖሊስን የምርመራ መዝገብ የመረመው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ዳይሬክተሮች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የ8 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡
4ኛ እና 5ኛ ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት ግን በዋስ ወጥተው በውጭ ሆነው ምርመራው ቢቀጥል የሚያደርሱት ተጽኖ አይኖርም በማለት በ10 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ችሎቱ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ
Exit mobile version