Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የታጠቁ ኃይሎች ሰላማዊ መንገድ በመምረጥ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል -ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ሰላማዊ መንገድን በመምረጥ በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ አሀራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ነገ በሲዳማ ክልል የሚጀመረውን አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር÷ ትጥቅ ያነሱ ወገኖች በምክክር ሂደቱ በመሳተፍና በመመካከር ጥያቄዎቻቸውን እንዲያነሱ ተደጋጋሚ ጥሪ ከማቅረብ ባሻገር ለሂደቱ ስኬት ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በዚህም ከለላ በመስጠት፣ ሰላማዊ መንገድ መከተልና የአደራዳሪዎችን ተሳትፎ በማካተት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሀገራዊ እውቀትና ባህል መሰረት ግጭቶች የሚፈቱባቸው መንገዶች በመኖራቸው አማራጩን ተጠቅሞ በምክክር ሂደቱ መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው፤ መገናኛ ብዙሃንም ግንዛቤውን በማስጨበጥ ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ከምክክር ውጪ ያለው አማራጭ ሀገርን የሚያፈርስ፣ ኢኮኖሚን የሚጎዳና ውድ የሆነውን የሰው ሕይወት የሚቀጥፍ በመሆኑ የተሻለውን መንገድ መከተል ውጤታማ እንደሚያደርግ መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

በመሆኑም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሰላማዊ መንገድ በመምረጥ ወደ ምክክር ሂደቱ እንዲመጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው ፥ ጥሪውን ተቀብሎ ለሚመጡ አካላት ኮሚሽኑ ሕጉን ተከትሎ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያመቻች መሆኑን ጠቁመው፤ አሁንም እድሉን ሊጠቀሙ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሲዳማ ክልል ነገ በሚጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ከ1ሺህ 800 በላይ ዜጎች የሚሳተፉ ሲሆን÷ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንደሚሳተፉ ተመልክቷል፡፡

Exit mobile version