በማዕከል እና ክልሎች ባሉ የወርቅ ግዥ ቅርንጫፎች በኩል የሚገዛውን ወርቅ በተመለከተ የተደረገ የዋጋ ማሻሻያ መመሪያ ቁጥር ከማዳ 2/2016
መግቢያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ያደረገው ስርነቀል ማሻሻያ ለወርቅ አቅራቢዎች ዘላቂ ማበረታቻ እንደሚፈጥር በመታመኑ እና የወርቅ አቅርቦትን በዘላቂነት ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ
ከባህላዊ የወርቅ ምርት ዘርፍ አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በዘላቂነት እንዲገኝ ለማስቻልና እንዲሁም አቅራቢዎችን ሊያበረታታ የሚችል አሰራር መተግበር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በመሆኑም ይህ የውስጥ አሰራር መመሪያ ተሸሽሎ ወጥቷል
አንቀጽ 1 አጭር ርዕስ
ይህ ማሻሻያ ደንብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግብይት ዋጋን አስመልክቶ የተሻሻለ የአሰራር መመሪያ ቁጥር 2/2016 ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
አንቀጽ 2፡ ማሻሻያ
የወርቅ ዋጋን አስመልክቶ ከሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ውሎ በነበረው መመሪያ ቁጥር ከማዳ/ 865/2024 ውስጥ የተካተቱ አንቀጾች በሚከተሉት ድንጋጌዎች ተተክተዋል፣
ሀ) የወርቅ መግዣ ዋጋ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ-ገፅ (Website) ላይ በየዕለቱ በሚገለጸው የውጭ ምንዛሪ መሸጫ ተመን (Selling Rate) ላይ ተመስርቶ የሚወሰን ይሆናል፣
ለ) ወርቅ አቅራቢ ማህበራትን /ግለሰብ ነጋዴዎችን ለማበረታታት ታስቦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው አሠራር መሠረት አቅራቢዎች ላቀረቡት ወርቅ 95 በመቶ ክፍያ በቅድሚያ በመውሰድ እና ቀሪውን 5 በመቶ የዋጋ መጠበቂያ በማድረግ ወርቁን ለግዢ ማዕከላት ካስረከበበት ቀን ጀምሮ በ30 ተከታታይ ቀናት ከተመዘገበው ዋጋ መርጠው በሚያቀረቡት መሰረት ክፍያ ያገኛሉ፡፡
30ኛው ቀን የበዓላት ወይም የሳምንቱ የእረፍት ቀን ከሆነ እስከሚቀጥለው የስራ ቀን ድረስ ዋጋ መምረጥ የሚችሉ ሆኖ ከ30 ቀናት በኋላ ደንበኛው ካልቀረበ በ31ኛው ቀን በሚውለው የወርቅ ዋጋ ባንኩ የሚገዛ ይሆናል፣
ሐ) ትላልቅ አምራቾች/ኩባንያዎች ከወርቅ ሽያጭ ከሚያገኙት ገቢ 50 በመቶ በውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው መጠቀሚያ እንዲሁም ቀሪውን 50 በመቶ በዕለታዊ የውጭ ምንዛሪ መሸጫ ተመን (Selling Exchange rate) እየታሰበ ክፍያ ያገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሰረት በዚህ መልክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ይዘው መጠቀም የሚቻለው ለአንድ ወር ጊዜ ብቻ ቢሆንም፣ ወርቅ አምራች ኩባንያዎችን ማበረታታት እንዲቻል ከወርቁ ሽያጭ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ለ3 ወራት ይዘው የሚጠቀሙ ይሆናል፡፡
በዚህ መልክ የሚቀርበው ወርቅ በብሔራዊ ባንክ እና በወርቅ አምራች ኩባንያዎች መካከል በሚደረገው ውል መሰረት በባንኩ በኩል ወደ ውጭ እየተጓጓዘ የሚነጠር ይሆናል፣
መ) በአንድ ጊዜ ከ250.01 ግራም ጀምሮ እስከ 25 ኪሎ ግራም ወርቅ ለሚያቀርቡ ወርቅ አቅራቢዎች በባንኩ የውስጥ አሰራር መመሪያ መሰረት ወጪያቸውን እንዲሸፍኑ ለማስቻል ማበረታቻ እየተደረገ ግዢ ይፈጸማል፣
ሠ) በአንድ ጊዜ ከ25.01 ኪሎ ግራም በላይ ከአቅራቢዎች በመሰብሰብ (Aggregator) ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለሚያቀርቡ አቅራቢዎች በባንኩ የውስጥ አሰራር መመሪያ መሰረት ወጪያቸውን ሸፍነው ገቢ የሚያገኙበት ከፍ ያለ ማበረታቻ እየተደረገ ግዢ ይፈጸማል፡፡
ረ) በዚህ መመሪያ ፊደል (ለ)፣(መ) እና(ሠ) የተጠቀሱት ማበረታቻዎች ለትላልቅ አምራች ኩባንያዎች (ፊደል ሐ) ተፈጻሚ አይሆኑም፡፡
አንቀጽ 3፡ ተፈጻሚነት
ይህ ማሻሻያ ከነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡