Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ክርስቲያኖ ሮናልዶ አልናስር የመጨረሻ ክለቡ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) ክርስቲያኖ ሮናልዶ አሁን እየተጫወተበት ያለው የሳዑዲው አልናስር ክለብ የመጨረሻው ሊሆን እንደሚችል ከፖርቹጋል ቴሌቪዥን ጋር በነበረው ቆይታ ፍንጭ ሰጥቷል፡፡

የ39 ዓመቱ የእግር ኳስ ኮከብ ከማንቼስተር ዩናይትድ ቆይታ በኋላ በፈረንጆቹ 2023 ጥር ወር ወደ ሳዑዲ ፕሮ ሊግ ማቅናቱ ይታወሳል፡፡

የእግር ኳስ ሕይወቱን ወደ ጀመረበት የሀገሩ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን ተመልሶ ጫማውን ሊሰቅል እንደሚችል በርካቶች ቢተነብዩም ሮናልዶ ግን አልናስር የመጨረሻው ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

እግር ኳስ መጫወቱን መቼ እንደሚያቆም እርግጠኛ ባይሆንም÷ በመጪዎቹ ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ጫማ ሊሰቅል እንደሚችል አመላክቷል፡፡

የተጫዋችነት ሕይወቱ ሲያበቃ አሰልጣኝ መሆን ይፈልግ እንደሆነ ለቀረበለት ጥያቄም÷ ቀጣይ ሕይወቱን ከእግር ኳስ ውጪ በሆነ ሥራ እንደሚያሳልፍ መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።

አሁን ላይ በአልናስር እየተጫወተ የሚገኘው ሮናልዶ÷ ቀደም ሲል በማንቼስተር ዩናይትድ፣ ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ ስኬታማ ጊዜ አሳልፏል፡፡

የአምስት ጊዜ የባሎን ዶር እና የአምስት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ አሸናፊም ነው፡፡

Exit mobile version