Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ም/ጠ/ሚ ተመስገን ሀገር ከጥቂት ጀምራ ለትልቁ ግብ እየሠራች መሆኗን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሀገር ትልቅ ተስፋ ይዛ ከጥቂት ጀምራ ለትልቁ ግብ እየሠራች መሆኗን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በሶማሌ ክልል ሸቤሌ ዞን ቤር ኣኖ ወረዳ በመሰኖ የለማ የሩዝ ምርትን ጎብኝተዋል፡፡

አቶ ተመስገን በሸበሌ ዞን ምዕራብ ጎዴ አካባቢ በመስኖ የለማ የሩዝ ምርት አሰባሰብን ያስጀመሩ ሲሆን በዚሁ ወቅት÷ የግብርናው ዘርፍ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት ከትንሽ ጀምሮ ማሳደግንና ማስፋፋትን በተግባር እያሳ መሆኑንም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ በበኩላቸው÷ በመስኖ ለምቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰበሰበው የሩዝ ምርት በቀጣይ የክልሉን የማምረት አቅም አመላክቶናል ብለዋል።

ጅማሮው ለክልሉ የግብርና ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው÷ ያለንን መሬት በመጠቀም በቀጣይ በሚተገበሩ የግብርና ስራዎች ራስን መቻል የሚለው እሳቤ በተግባር ይረጋገጣል ነው ያሉት፡፡

የሩዝ ምርት ፍላጎትን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተሠራ መሆኑን የገለጹት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ አሁን ላይ 50 በመቶውን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ችለናል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

ምርትና ምርታማነትን በማጠናከር ረገድም ከስንዴና የቢራ ገብስ ቀጥሎ በሀገር ውስጥ የምንሸፍነው የሩዝ ምርት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በፍሬሕይወት ሰፊው

Exit mobile version