የሀገር ውስጥ ዜና

የሩዝ ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ለማሟላት ርምጃችን ፍሬያማ ሆኗል- አቶ አደም ፋራህ

By amele Demisew

August 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩዝ ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ለማሟላት የጀመርናቸው ርምጃዎች ፍሬ እያፈሩ ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በሶማሌ ክልል ሸቤሌ ዞን ቤር ኣኖ ወረዳ በመሰኖ ለምቶ እየተሰበሰበ ያለ ሩዝን ጎብኝተዋል፡፡

አቶ አደም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፈን ስንዴ ወደ ውጭ የመላክ ትልማችን በተሳካ ማግስት÷ የሩዝ ምርት ፍላጎታችንን በሀገር ውስጥ ለማሟላት የጀመርናቸው ርምጃዎች ፍሬያማ ሆነዋል ብለዋል፡፡

የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሥርዓታችን ለሀገራዊው የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከቱ በላይ÷ በአርብቶ አደርነት የምናውቃቸው አካባቢዎች በግብርና ሥራ ውጤታማ እያደረጋቸው ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሸበሌ ዞን ያየነው በመስኖ ሩዝ የማምረት ሀገራዊ የሙከራ ፕሮግራምም ትምህርት የተገኘበትና እስከ 30 ሚሊየን ሄክታር መልማት የሚችል ለሩዝ ተስማሚ ሥነ-ምኅዳር ላላት ሀገራችን ተስፋ ፈንጥቋል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ለሩዝ ምርት ያለውን ተስማሚ ሁኔታ አጥንቶ ወደ ስራ በመግባቱ÷ በ4 ዞኖችና በ7 ወረዳዎች ሩዝን በመስኖ ለማልማት የተደረገው ሙከራ ውጤታማ ሆኗል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ከስንዴ እና ከቢራ ገብስ ቀጥሎ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማርካት ሩዝን ወደ ውጭ ለመላክ የያዘችው ትልም እንደምታሳካው በሸበሌ ዞን ያለው የሩዝ ማሳ ምስክር ሆኗል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም የጎደለውን በመሙላት እና ስኬቶችን በማስቀጠል በክልሉ የታየው እምርታ ከኢትዮጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ብሎም ለዓለም በረከት እንዲሆን በትኩረት እንሠራለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡