አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝቦች እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ግንባታን በማጠናከር የምክር ቤቱ ተልእኮ እንዲሳካ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባበሪ ኮሚቴ የቀረበለትን የጽሕፈት ቤቱን የ2017 በጀት ዓመት እቅድ በመገምገምና ግብዓት በማካተት አጽድቋል፡፡
በዚሁ ወቅት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር÷ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለጥናትና ምርምር ሥራዎች ሰፊ ትኩረት በመስጠት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመተሳሰብና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ሕብረብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጠናከር እና የኢትዮጵያ የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት እንዲዳብር የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የሕዝቦች እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ግንባታን በማጠናከር የምክር ቤቱ ተልእኮ እንዲሳካ በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ከባለድሻ አካላት ጋር የተጀመሩት ሥራዎች ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸው÷ የተቋሙን አፈጻጸምና የአገልግሎት አሰጣጥ በጊዜ፣ በመጠንና በጥራት ከፍ ማድረግ የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡