የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል 806 ሺህ 476 ሔክታር መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፈነ

By ዮሐንስ ደርበው

August 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016/17 የመኸር ምርት ወቅት 806 ሺህ 476 ሔክታር መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በምርት ዘመኑ የስንዴ ምርታማነትን በሔክታር ወደ 41 ነጥብ 2 ኩንታል ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑንም ነው ቢሮው ያስታወቀው፡፡

ክልሉ ለስንዴ ሰብል ልዩ ትኩረት መሰጠቱን እና በዚህም በየዓመቱ አዳጊ ውጤቶች መመዝገባቸውን የቢሮው መረጃ አመላክቷል፡፡

በምርት ዘመኑ የታቀደውን ምርት ለማሳካትም ርብርብ እየተደረገ ሲሆን÷ ምርታማነቱን ለማሳደግ በመጠንና በወቅቱ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱ ተገልጿል፡፡

የተሻለ የዝናብ ሥርጭት በመኖሩ በምርት ዘመኑ ለማግኘት የታቀደውን 43 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ማሳካት እንደሚቻል ይጠበቃል ብሏል ቢሮው፡፡