የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ጥላሁን ከበደ የሕዝብ ትስስርን በማጠናከር ክልሉን ማሳደግ እንደሚገባ አስገነዘቡ

By Shambel Mihret

August 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥላቻን በፍቅር፤ ጥርጣሬን በእምነት በመቀየር የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር ክልሉን ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ “ከነሐሴ እስከ ነሐሴ” በሚል ርዕስ የክልሉን ምስረታ ሂደት እና የተከናወኑ ዐበይት ተግባራት የሚዳስስ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጓል።

በዚሁ ወቅት ሕዝባችንን ተጠቅመን በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል ያሉት አቶ ጥላሁን÷ ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ፀጋዎች አሟጥጠን በመጠቀም ኢኮኖሚያችንን ማሻሻል አለብን ብለዋል፡፡

የፀጥታ ስጋት የሆኑ ቀጣናዎችን አስቀድሞ በመለየት መሥራት እንደሚገባ አሳስበው÷ ክልሉን የብልጽግና፣ የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የክልሉ ሕዝብ እና አመራሮች የሚጠበቅባቸው እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በአበበች ኬሻሞ