አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የቦይንግ የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት በመጪው ጥቅምት ሥራ እንደሚጀምር የጽሕፈት ቤቱ ዋና ኃላፊ ሄኖክ ተፈራ አስታወቁ፡፡
ቦይንግ የአፍሪካ ዋና ጽሕፈት ቤቱን በአዲስ አበባ የከፈተው ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ስኬታማ ሥራ ከግምት በማስገባት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ የፊታችን ጥቅምት ሥራ እንደሚጀምር ገልጸው÷ የጽሕፈት ቤቱ መከፈት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከልነቷን አጠናክራ ለማስቀጠል ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥርላት ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ቦይንግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተመተባበር በተለይም የአውሮፕላን ክፍሎች (ዕቃዎች) በጋራ ለማምረት የሚያስችል ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ እንደሚተኩርም አመላክተዋል፡፡