አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የተመራ የክልል ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በማኦ እና ኮሞ ልዩ ወረዳ በመገኘት የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኝቷል።
አመራሮቹ በልዩ ወረዳው እየተከናወነ ያለውን የመኸር እርሻ ሥራ እንቅስቃሴን የተመለከቱ ሲሆን÷ በልዩ ወረዳው ሚሚ የኮቦ ቀበሌ በክላስተር እየለማ የሚገኘውን የበቆሎ ሰብል ጎብኝተዋል።
በወቅቱ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን÷ በ17 ሚሊየን ብር የተገነቡ ተቋማትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉ ሲሆን የጤና ጣቢያ ግንባታ የመሠረት ድንጋይም አስቀምጠዋል።
የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከማል እንድሪስ በበኩላቸው÷ በወረዳው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ተቋማት በጸጥታ ችግር ምክንያት መውደማቸውን አስታውሰዋል፡፡
መንግሥት ከህዝቡ ጋር በመተባበር ተቋማቱን እንደገና በማደራጀት የልማት ስራዎችን ማስቀጠል ችሏል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡