የሀገር ውስጥ ዜና

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 1ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እየተከበረ ነው

By Shambel Mihret

August 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 1ኛ ዓመት ታሪካዊ የምስረታ በዓል በወላይታ ሶዶ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

ክልሉ በሕዝቦች ነፃ ፍላጎትና ይሁንታ ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ህዝበ ውሳኔ ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ በተካሄደ ታሪካዊ የምስረታ ጉባኤ የፌደሬሽኑ 12ኛው ክልል ሆኖ በይፋ መመስረቱ ይታወሳል፡፡

በረዥም ዘመን አብሮነት የተጋመዱና የተሳሰሩ 32 ነባር ብሔረሰቦችና ሌሎች ሕዝቦች ነፃ ፈቃድ ቀዳሚው የብዝኀ ሕዝቦች ክልል ሆኖ ከተመሰረተም አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡

እየተከበረ ባለው የ1ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉ የክልሉ የአንድ አመት ጉዞ በጥልቀት ይዳሰሳል ተብሏል፡፡

በመርሐ ግብሩ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ፣ የፓናል ውይይት እና ሌሎች ተያያዥ ኩነቶች እንደተካተቱ እና በክልሉ ምስረታ ወቅት የፀደቀው የክልሉ ህገ መንግስት ህትመት እንደሚሰራጭም ተገልጿል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አውደ ርዕዩን መርቀው የከፈቱ ሲሆን÷ አውደ ርዕዩ በክልሉ የአንድ ዓመት ጉዞ የተከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኩነቶችን የቃኘ ነው ተብሏል፡፡

በምስረታ በዓሉ ከርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተጨማሪ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎችና አባላት፣ የዞን አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባቶች፣ ምሁራን እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በአበበች ኬሻሞ