የሀገር ውስጥ ዜና

ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ላይ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተመለከተ

By amele Demisew

August 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአረጋዊያን እና አቅመ ደካሞች የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች ርክክብ ተደርጓል፡፡

በክልሉ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር የታደሱና የተገነቡ 52 የአቅመ ደካማ ወገኖች መኖሪያ ቤቶች ተመርቀው ለተጠቃሚዎች የተላለፉ ሲሆን÷ ለ 2 ሺህ አቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

መኖሪያ ቤቶቹን መርቀው ያስተላለፉት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ÷አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ላይ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ዕዳን ሳይሆን ምንዳን ለማውረስም ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ምቹ መኖሪያን በመፍጠር የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች የሚያቃልሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዘንድሮ ብቻ በክረምት በጎ ፈቃድ 117 የአቅመ ደካማ ዜጎች መኖሪያ ቤቶችን ለማደስ ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል።

በሌላ በኩል የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት ሁሉም ዜጋ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡