የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አረጋ ከበደ በሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ

By Shambel Mihret

August 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ፡፡

በክልሉ በተጠቀሰው አካባቢ ትናንት በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የ10 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ስምንት ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ÷በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው ከአደጋዉ የተረፉትን ወገኖች ለማቋቋም የአካባቢዉ አመራርና ህዝብ እንዲሁም ሌሎች አካላት እያደረጉ ያለዉን ድጋፍ አጠናክረው እንድትቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ መንግስትም ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም እና አማራጭ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡