አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ እንደገለጹት÷በገበያ ላይ ጠንካራ የአቅርቦትና ግብይት ሰንሰለት ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ጥራታቸውን የጠበቁ ግብዓቶችን ከማቅረብ ረገድ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ድርጅቱ መንግስት ቅድሚያ በሰጣቸው ዘርፎች ለተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃና የተለያዩ ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከኢንዱስትሪ ግብዓቶችና ውጤቶች ሽያጭ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ቀልጣፋና ውጤታማ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ የአቅርቦት ሰንሰለት አሰራርን ለመተግበር እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ