Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የንግዱን ማህበረሰብ ጥያቄ የመለሰ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የንግዱን ማህበረሰብ ጥያቄ የመለሰ ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው አገር አቀፍ የንግድ ሳምንት አውደ ርዕይ በይፋ ተከፍቷል፡፡

አውደ ርዕዩ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን÷ገዥና ሻጭን ማገናኘት፣ በዘርፉ ያለውን አቅም ማሳየት እንዲሁም ንግድን በተመለከተ ግንዛቤ የሚያሳድጉ ውይይቶች የሚደረጉበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷የኢትዮጵያን ዕድገት ዘላቂ እና አስተማማኝ ለማድረግ ዘመናዊ የንግድ ስርዓት መዘርጋት ይገባል፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ስርዓት ተወዳዳሪ ማድረግ፣ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ላይ የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

መንግሥት የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑንም በመግለጽ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻያ እየተፈጠሩ ካሉ ምቹ ሁኔታዎች መካከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማሻሻያው የንግዱን ማህበረሰብ ጥያቄዎች የመለሰ ነው ብለዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮችን በጥናት በመለየትና የተሻሻሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ለንግዱ ዘርፍ መዘመንና መጠናከር ተግባራዊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Exit mobile version