አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ዘላቂ የከተሞች እድገትና ትስስርን የሚያሳልጥ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።
በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በ31 ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ እንዳሉት÷ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ከተሞች የሰፋው የኮሪደር ልማት ስራ ከተሞችን ለኑሮ ተስማሚ የሚያደርግ ነው፡፡
የኮሪደር ልማቱ ከተሞች ዘላቂ የሆነ ፕላን እንዲኖራቸውና በየጊዜው ለማስፋት ሲባል የማፍረስ ሂደቶችን የሚያስቀር መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
በተጨማሪም ዘመናዊ እና ስማርት ከተሞችን በመፍጠር ዘላቂ የከተሞች እድገትና ትስስርን እንደሚያሳልጥ ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ከተሞች በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተሉ ከማድረጉም ባሻገር ንጹህ እና አረንጓዴ ገጽታ እንዲላበሱ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
ከኮሪደር ልማት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ከተሞችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትሯ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎችም የዜጎችን የልማት ተሳትፎ እንዲነቃቃ እያደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡