የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከ26 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

By Mikias Ayele

August 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2016 በጀት ዓመት ከ26 ነጥብ 46 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የፋይናንስ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደመረ አሰፋ እንደገለፁት÷ ገቢው የተሰበሰበው ከኃይል ሽያጭ፣ ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ እና ከባለፈው ዓመት ከዞረ የኃይል ሽያጭ እንዲሁም ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ነው፡፡

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 27 ነጥብ 46 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከ26 ነጥብ 43 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የዕቅዱን 96 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ19 ነጥብ 8 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማጠናከር፣ ወቅቱን የጠበቀ ክትትል በማድረግ እና ከደንበኞች ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ በመሰራቱ በገቢ አሰባሰብ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመደበኛ ወጪዎች ከራሱ ገቢ ሰብስቦ መሸፈን የማይች እንደነበር ያስታወሱት ስራ አስፈፃሚው÷ አሁን ግን መደበኛ ወጪውን ሸፍኖ በራሱ ገቢ የካፒታል ፕሮጀክቶቹን ለመሸፈን ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በቀጣይ የገቢ አማራጮችን በማስፋትና ወጪ በመቀነስ የገቢ አሰባሰቡን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ መናገራቸውን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡